“ምረጪ – ወይ እገልሻለሁ ወይ እደፈርሻለሁ”- በኢትዮጵያ ጦርነት ውስጥ የጥቃት ክሶች ተበራከቱ

በ ማይክል ጆርጂ ተፅፎ በ Horn Anarchists ተተረጎመ

Download PDF

ሃምዴት ፣ ሱዳን (ሮይተርስ) – ወጣቷ ቡና ሻጭ ተከዜ ወንዝ ላይ አንድ ኢትዮጵያዊ ወታደር ከቤተሰቧ እና ወዳጆችዋ ጋር እንደነጠላት እና ለይቶ ወስዷት አስጨናቂ ምርጫ እንደሰጣት ትናግራች፡፡

የ 25 ዓመቷ ወጣት ከኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ተሰዳ አሁን ባለችበት በሱዳን ሃምዳዬት የስደተኞች ካምፕ ለሮይተርስ “’ምረጪ – ወይ እገልሻለሁ ወይ እደፈርሻለሁ’ አለኝ” ስትል ተናግራለች፡፡

በታህሳስ ወር ወደ ስደተኛ ካምፑ ስትመጣ ያከማት ሃኪም ቴዎድሮስ ተፈራ ሊሙህ እርግዝናን እና በጾታዊ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎችን ለማስቆም ክኒን እንደሰጣት እና  ወደ ሳይኮቴራፒስት እንደ መራት ለሮይተርስ አረጋግጧል፡፡

ለሱዳን ቀይ ጨረቃ በበጎ ፈቃድኝነት እያገለገለ ያለው ዶ/ር ሊሙህ “ወታደሩ ጠመንጃ ደቅኖ አስገድዶ ደፈራት፡፡ ኮንዶም እንዳለው ስትጠይቀው ‹ለምን ኮንዶም ያስፈልገኛል?› ብሎ መለሰላት” ሲል ወጣቷ የነገረችውን ነግሮናል፡፡

አምስት የዓለም አቀፍ እና የኢትዮጵያ ዕርዳታ ድርጅት ሠራተኞች ተመሳሳይ የጥቃት ሪፖርቶች ከትግራይ እንደደረሷቸው ተናግረዋል፡፡ የተባበሩት መንግስታት በዚህ ሳምንት በክልሉ ውስጥ የሚደረጉ ወሲባዊ ጥቃቶች እንዲቆሙ ጥሪ አቅርቧል፡፡

ከቀረቡት “ከፍተኛ ቁጥር” ካላቸው የሚረብሹ ክሶች መካከል ዘመዶቻቸውን ለመድፈር የሚገደዱና መሰረታዊ አቅርቦቶችን ለማግኘት የግብረ ሥጋ ግንኙነት እንዲፈጽሙ የሚገደዱ ሰዎች እንዳሉ የተ.መ.ድ የግጭቶች ወቅት ወሲባዊ ጥቃት ልዩ ተወካይ ያሳለፍነው ሃሙስ በሰጡት መግለጫ ገልጸዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግሥት እና ወታደራዊ መዋቅሩ ስለ አስገድዶ መድፈር ሪፖርቶች ከሮይተርስ ለተጠየቁት ጥያቄዎች ወዲያውኑ መልስ አልሰጡም። የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ቀደም ሲል የመብት ጥሰቶችን ክደው ጣቶቻቸውን በአመፀኝነት ወደሚከሱት  የቀድሞ የክልሉ ገዥ ፓርቲ የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጪ ግንባር (ሕወሓት) ቀስረዋል።

የተባበሩት መንግስታት ልዩ ተወካይ ፕራሚላ ፓቴን በመግለጫው “በትግራይ ክልል በተፈጠረው ጠብ የሚሳተፉ አካላት ሁሉ በጾታዊ ጥቃት ወንጀል የዜሮ-መቻቻል ፖሊሲ እንዲወስዱ ጥሪዬን አቀርባለሁ” ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ የስደተኞች መጠለያ ካምፖች ውስጥ ያሉ ሴቶችና ልጃገረዶች በተለየ ዒላማ የተደረጉ ሲሆን የህክምና ማዕከላት ለድንገተኛ የእርግዝና ማቋረጫ እና በጾታዊ ግንኙነት የሚተላለፉ ኢንፌክሽኖች ምርመራ ለማድረግ እየቸገራቸው መሆኑን መግለጫው ያሳያል።

ሮይተርስ የአስገድዶ መድፈር ክሶችን በገለልተኝነት ማረጋገጥ አልቻለም። አብዛኛዎቹ ሚዲያዎች ከትግራይ ታግደዋል ፣ የእርዳታ ድርጅቶች ተጎጂዎች ጋር ተደራሽ ለመሆን ተቸግረዋል፣ የግንኙነት መስመሮችም ለሳምንታት ተቋርጠው ቆይተዋል።

ዩኒፎርም ለባሽ አጥቂዎች 

ሮይተርስን ያነጋገረችው የ 25 አመቷ ሴት አጥቂዋ የኢትዮጵያ የፌደራል ጦር ዩኒፎርም ለብሶ እንደነበር ትናገራለች፡፡

አምስቱ የእርዳታ ሰራተኞች በበኩላቸው ሌሎች ሴቶች አጥቂዎቻቸው የአማራ ክልል ሚሊሻ ተዋጊዎች እና የኤርትራ ወታደሮች መሆናቸውን ገልፀዋል። ሁለቱም ከአብይ ሰራዊት ጋር ተባባሪ መሆናቸው ይታወቃል። ሮይተርስ ወጣቷን ያጠቃትን ሰው ማንነት መለየት አልቻለም።

የአብይ ቃል አቀባይ ፣ የትግራይ ጊዜያዊ ገዥ ፣ የክልሉ ዋና ከተማ ከንቲባ ፣ የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የኢትዮጵያ ጦር ቃል አቀባይ በአስገድዶ መድፈር ክሶች ዙሪያ አስተያየት እንዲሰጡ ቢጠየቁም ወዲያውኑ መልስ አልሰጡም። ሮይተርስ የህወሓትን ተወካዮች ማግኘት አልቻለም።

የአማራ ክልል ቃል አቀባይ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ በበኩላቸው በስልክ ለሮይተርስ “ስለዚያ ምንም መረጃ የለኝም” ብለዋል።

በደርዘን ከሚቆጠሩ የአይን ምስክር ቃለመጠይቆች፣ ዲፕሎማቶች እና ከአንድ የኢትዮጵያ ጄኔራል ተቃራኒ በሆነ መልኩ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ የኤርትራ ወታደሮች በኢትዮጵያ ውስጥ መኖራቸውን አስተባብለዋል፡፡

“ሴት ለምን ይደፈራል?”

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በመቀሌ የተካሄደው የፀጥታ አስከባሪ ባለሥልጣናት ስብሰባ በኢትዮጵያ መንግሥት ቴሌቪዥን በተላለፈበት ወቅት፣ አንድ ወታደር ከተማዋ በፌዴራል ኃይሎች ከተያዘች በኋላም እየደረሱ ስላሉ ጥቃቶች ተናግሯል።

“ትናንት ተናድጄ ነበር። መቀሌ ከተማ ውስጥ ሴት ለምን ይደፈራል? በጦርነቱ ጊዜ ቢከሰት አያስደነግጥም ነበር … ግን ትናንትና ዛሬ የአካባቢው ፖሊሶች እና የፌደራል ፖሊሶች ባሉበት ሴቶች ይደፈራሉ።” ሲል ያልታወቀ ወታደር ተናግሯል።

የአከባቢው ባለሥልጣናት ወታደሮች መመርመር ወይም ለፍርድ መቅረብ ይችሉ እንደሆነ አስተያየት ቢጠየቁም ወዲያውኑ ምላሽ አልሰጡም።

የስደተኞች ካምፕ ሀኪም የሆነው ቴዎድሮስ ስላያቸው ሌሎች ሁለት የአስገድዶ መድፈር ጉዳዮችን ገልጻል። ከትግራይ ራውያን ከተማ ያመለጠች አንዲት ሴት በሯን ሲያንኳኩ የአማራ ልዩ ሀይል መሆናቸውን ስለለየቻቸው ሶስት ወታደሮች ትናግራለች። ቤቷ መግባት ስትከለክላቸው ሰብረው ገብተው ጥቃት እንደሰነዘሩባትም ተናግራለች።

በውቅሮ ከተማ ውስጥ የሚሰሩ የእርዳታ ሰራተኞች አንድ ሚስቱ በኤርትራዊ ወታደሮች ሲትደፈር ተንበርክኮ እንዲያይ ስለተገደደ ሰው ለሮይተርስ ተናግረዋል።

በዓዲግራት አንድ የህክምና ሰራተኛ በወታደሮች ቡድን  የተደፈሩ ስድስት ሴቶችን ማከሙን ገልጾ ከደፈሯቸው በኋላ እርዳታ ለማግኘት እንዳይሞክሩ እንዳስጠነቀቋቸው ተናግሯል። ከቀናት በኋላ ወደ ፊት መጥተው ያጋጠማቸውን ለመንገር ድፍረትን ቢያገኙም፣  እነሱን ለማከም የሚያስችሉ መድኃኒቶች እንዳልነበሩ ሃኪሙ ተናግሯል።

በመቀሌ ከተማ አንድ ሰው አንዲት የ19 አመት ታዳጊን መድፈር እንዲያቆሙ ወታደሮችን ሲለምን መደብደቡን ለሁለቱም ተጎጂዎች ህክምና ያደረገው የህክምና ባለሙያ ገልጿል። በመቀሌ የሚገኝ ኤልሻዳይ የሚባል የበጎ አድራጎት ድርጅት የአስገድዶ መድፈር ሰለባ ለሆኑ ሴቶች 50 አልጋዎች ማዘጋጀቱን ገለጿል።